‘የብርሃን ፈለጎች’ ከዓለማየሁ ገላጋይ ስራዎች ውስጥ የመጀመሪያው ንባቤ ነው። ግሩም ታሪክ ነው የነገረን። ልጅነት፣ አፍላነት፣ እና ጎርምስና በሁለት አውዶች ውስጥ እንዴት እንደተሰባጠሩ እናስተውላለን። እጦትን (loss) መላመድን (adapting)፣ ፍለጋን፣ ፍቅርን እና ስህተትን ከእነ ውጥንቅጡ ያሳየናል።
የመጽሐፉ ኋለኛ ምዕራፎች ስለ ፍልስፍና በጥቂቱ አስተዋወቀው ባለታሪኩ ያለፈበትን የማንነትን ፍለጋ ውጣ-ውረድ ያስቃኛሉ። ይህ ዓይነት አቀራረብ ብዙም ባይስበኝም (ልብ-ወለድ የግድ አስተማሪና ሰባኪ መሆን አለበት ብዬ አላምንም) እንደምንም ተወጥቼዋለሁ። የእነዚህ ምዕራፎች አተራረክ በእርግጥ ግራ አጋቢም ነበር። ተራኪው የቱጋ በዕውኑ፣ የቱጋ ደግሞ በሰመመን እና በቅዠት ዓለም እንደሚያወራና እንደሚከውን ግር ይላል። ይህ ንባቤን አደነቃቅፎብኛል። ደራሲው እንደዚህ ያለውን የተራኪውን ውጥረት ቶሎ ጨርሶ ታሪኩን በደንብ ማሰር ይችል ነበር። ስለሆነም በድህረ-ታሪክ ለመጨረስ ተገዶአል።
ተራኪው ከወላጆቹ ጋር ያለው ግንኙት ብዙ ሊጻፍበት የሚቻል ጉዳይ ነው። ግዜ ካለኝ በሰፊው እጽፍበት ይሆናል። ለአሁኑ ግን ከሞላ ጎደል ጥሩ ንባብ ነበር ብዬ ላብቃ።